ማንኛውንም ነገር ለማምረት ማወቅ ያሉብን 7 ደረጃዎች

ወደ ፊት የሆነ ነገር በማምረት (ሳሙና ፣ ሽቶ ፣ ዘይት) የራሳችሁን ስራ መስራት ፍላጎት ካላችሁ ወይም በፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥራችሁ የመስራት ፍላጎት ካላችሁ ይህ የመነሻ ሀሳብ ይጠቅማችዋል። መልካም ንባብ።አለማችንን ፍፁም ወደ ሌላ ደረጃ ያሸጋገራት የኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት (Industrial Revolution) ነው። ከዝያ በዋላም የሰው ልጆች ተፈጥሮ የሰጠችንን ፀጋ በመጠቀም በይበልጥ ማረት ብሎም ሰው ሰራሽ ነገሮችን በመፍጠር ወደ ምርት ቀይረናል።


ዛሬ በአለማችን የትየለሌ ምርቶች ተመርተዋል:: እስቲ ዞር ብላችሁ አከባቢያቹን ቃኙ ምን ያልተመረተ ነገር አለ?:: ከያዝነው ስልክ እስከ ረገጥነው ምንጣፍ ወይም ወለል የተመረተ ነገር ነው::
ታድያ ማንኛውም ነገር ለማምረት ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ፋብሪካዎች ምን አይነት ደረጃዎችን ያልፋሉ ?:: ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ እና ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው ሽፈራው የጻፏቸውን መጽሐፎች መሰረት በማድረግ ለአቀረረብ ምቹ በሆነ መልኩ እንደሚከተለው እንመለከታለን::


1. ጥሬ ሐብት ማግኘት (Finding the right Raw material )


ማንኛውንም ነገር ለማምረት ዋናው መነሻው ጥሬ ሐብት (raw material) ነው። ይሄን ሀሳብ ለመረዳት እንዲቀለን ሁሌ እያፈላን የምንጠጣውን ቡና እንደ ፋብሪካ እናስበው። ቡና ለማፍላት ምን ያስፈልገናል? ቡናው አይደል ይሄ ጥሬ ሐብት እንለዋለን:: ወጥ ለመስራትስ ምን ምን (ingredients) ትጠቀማላችሁ ? ያ ማለት ነው።


ሳሙና ለማምረት የሳሙና መስሪያ ኬሚካሎች ፣ ስኳር ለማምረት የሸንኮራ አገዳ ፣ የኑግ ዘይት ለማምረት ኑግ ፣ ሽቶ ለማምረት እጽዋት ያስፈልጉናል። እናም ይሄን ጥሬ ሐብት በመግዛት ለምርት እንዳያስቸግረን እናከማቻለን። ወይም ድርጅታችንን ጥሬ ሐብቱ ያለበት ቦታ እንተክላለን::


የወርቅ ፣ የነዳጅ ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ስናስብ ጥሬ ሐብቱ ያለበት ቦታው ድረስ በመሄድ ፋብሪካ ይተከላል:: ወይም ለሌሎች ምርቶች ጥሬ ሐብቱ ተጉዞ “ፕሮሰስ” ወደ ሚደረግበት ቦታም ይጠራቀማል::


2. ጥሬ ሐብቱን ማዘጋጀት (Raw material preparation)፡


ቡና ከማፍላታችን በፊት ቡናውን መፈልፈል እና ማጠብ አለብን አይደል ? የትኛውም ነገር ከመመረቱ በፊት ለምርት አመቺ እንዲሆን መዘጋጀት አለበት። የቆሸሸው መታጠብ ፣ የረዘመው በልክ በልክ መቆረጥ ይገባዋል (washing or cleaning, size reduction (cutting) ጥሬ ሐብቱ ሌሎች ተመሳሳይ ሂደቶችን ያልፋል ። ይሄንንም ሂደት ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ ፊዚካላዊ ሂደት (physical process) በማለት ይጠሩታል። በዚህ ሂደት የተለያዩ የማጠብያ ፣ የመቆራረጫ ማሽኖች ያስፈልጉናል ማለት ነው።

3. ጥሬ ሐብቱን መለወጥ (Chemical Transformation) ፡


ጥሬ ሀብቱን ያዘጋጀነው ወደ ምርት ለመቀየር ነው ፤ ስለሆነም የተለያዩ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን በመቀላቀል ወደ ምንፈልገው ምርት እንቀይራለን ። ልክ ተወቅጦ የተዘጋጀ ቡናችንን የፈላ ውሃ ውስጥ ጨምረን ቡና እንደምናፈላው ማለት ነው:: ይሄ ምርታችንን የምናገኝበት ወሳኙ ደረጃ ነው:: ሂደቱም ባብዛኛው ኬሚካላዊ ለውጥ የሚታይበት በመሆኑ ኬሚካላዊ ሂደት (Chemical process ) ብለን እንጠራዋለን።
በዚህ ደረጃ ምርቱን የምንለውጥባቸው መቀመምያዎች (reactors) ያስፈልጉናል። በሂደቱም ምን እንደሚፈጠር (chemical reactions) የመረዳት ፣ የሙቀት (temperature) እና የመጠን ምጣኔ (material balance) እውቀት ሊኖረን ይገባል። ባብዛኛው እነዚህን ነገሮች አለማወቅ የምርታችንን ጥራት ያበላሻል። ይህ ደረጃ የምርቱ ሂደት ልብ ነው (heart of the process) ማለት እንችላለን።4. የተለወጠውን ምርት ካልተለወጠው መለየት (Separation of non-converted material)፡


ቡና ሲፈላ አስተውላችዋል?:: ሙሉ በሙሉ የተወቀጠው ቡና ፈልቶ አያልቅም አይደል?:: አቦል ፣ ጦና እና በረካ እየተባለ ከ1 እስከ 3 እየተመላለሰ ይጠጣል:: በምርት ደረጃም ተመሳሳይ ነገር እናያለን:: እናም እዚህ ጋር እናቶቻችን ምን ያክል ሳይንስ የገባቸው ነቄዎች እንደሆኑ አድንቀን እናልፋለን::


በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ አንድን ጥሬ ሐብት መቶ በመቶ ወደ ምርት የሚለውጥ ሂደት ወይም ማሽን የለም ተብሎ ይጠቀሳል (no 100 % efficiency)። ስለሆነም ወደ ምርት የተለወጠው ካልተለወጠው የተፈጨው ካልተፈጨው የተደባለቀው ካልተደባለቀው ይለያል:: ይህንንም ለመለየት ሴንሰሮች አንዳንዴም በሰው በመታገዝ መለየቱ ይከናወናል::

5. የምንፈልገውን ከማንፈልገው መለየት (Separation of unwanted & wanted products) ::


እዚህ ደረጃ ላይ ማምረት የምንፈልገውን ምርት ሌሎች ከምርቱ ጋር ከተቀላቀሉ አላስፈላጊ ነገሮች እንለያለን:: አላስፈላጊውን ከመስመር አስወጥተን አስፈላጊውን ወደ ቀጣይ ደረጃዎች ይዘን እንሄዳለን::


ምናልባት እንዳስፈላጊነቱ መልሶ የመጠቀም (recycling) አማራጭም ልንጠቀም እንችላለን::

6. ማድረቅ ማጣራት ማበጠር (Drying ) :


የተመረተው ምርት የሚታሸግ ከሆነ ማድረቅ ፈሳሽ ከሆነም ማጣራት ወይም ማጥለል ወዘተ... የመሳሰሉ ደረጃዎችን እናልፋለን::


7. የመጨረሻው ደረጃ


በዚህ የመጨረሻው ደረጃ ስር በርካታ የጥንቃቄ ስራዎች ይከናወናሉ በሶስት ከፍለናቸው ብናያቸው


ሀ. ጥራት ማጣራት ወይም ማረጋገጥ (Quality check up & Assurance ) : የሚበላ ነገር ከሆነ ለጤና ተስማሚ የሆነ ምርት ወደ ገበያ ማስገባት አለብን:: ከዝያ አለፍ ሲልም ተፈጥሮን የማይጎዳ ምርት ማምረት አለብን:: ለዚህ ሞራልም ህግም ያስገድደናል:: እናም የተመረተው ምርት ጥራቱን መጠበቅ መሆን ይገባል:: ለዚህም የተለያዩ ባለሙያዎች እና ማሽኖች ያስፈልጉናል::


ለ. ማሸግ እና ብራንድ ማድረግ (Packaging & branding) ፦ የተመረተውን ምርት ማሸግ የምርቱ ስም ማተም፣ የአምራቹ ድርጅት ምልክቶች (logo) ማድረግ ። የምርቱ ቀነ ገደብ (Expiration date) መጻፍ የመሳሰሉት በመጨረሻ ይከናወናሉ::ሐ. ማጠራቀም እና ማሰራጨት (Storage & Transportation ) : ያመረትነው ምርት ወደ ገበያ እስኪገባ የምናጠራቅምበት ቦታ ያስፈልገናል:: ወይም አየር ባየር ንግድ ላይ ከሆንም ምርቱን ወደ ፈላጊዎች ማጏጏዝ ስራችን ይሆናል::


ማንኛውም ምርት ሲመረት ባብዛኛው ከላይ የጠቀስናቸውን ደረጃዎች ያልፋል ተብሎ ሊቀመጥ ይችላል።


በመጨረሻ ምርታችን ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርጉ ነገሮች ምንድናቸው ?

  1. መጠንን ማወቅ (Material Balance or Management ) ፡ ማምረት የፈለግነውን ነገር መጠኑን ማወቅ። ምን ያክል ምርት ለማግኘት ምን ያክል ጥሬ ሐብት ያስፈልገናል የሚለው በጣም ወሳኝ ነው። ይሄም በባለሙያዎች በኬሚካል መሐንዲሶች ወይም በኬሚስትሪ ባለሙያዎች እና በዘርፉ ተያያዥ አውቀት ካላቸው ማወቅ ይቻላል። አንደመነሻ ከኢትንርኔት ወይም ከመፅሀፍ ላይ የምናገኛቸውን ቀመሮች ልንጠቀም እንችላለን።

  2. ጥራትን መጠበቅ (Quality Assurance) ፡ ጥራት የሌለው ምርት ተቀባይነቱ ዝቅተኛ ነው:: ጥራትን መጠበቅ ወሳኝ ይሆናል:: ይህም ከሞራል ብሎም ከህግ አንፃር አስገዳጅ ይሆናል።

  3. አከባቢን አለመበከል (Environment Friendly) ፡ በዚህ ወቅት የአከባቢ ጥበቃ ጉዳይ እጅግ ወሳኝ ነው። የምናመርታቸው ምርቶች ጤናን የማይጎዱ እና አከባቢን የማይበክሉ ካልሆኑ ጥርታችን ጥርጣሬ ውስጥ ይወድቃል፤ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነታቸው አናሳ እየሆነ መሄዱ አይቀርም።

  4. ኢኮኖሚያዊ አመራረትን መከተል (Economical Production)፡ ማንኛውም ምርት ትርፍ ካላስገኘ ከገበያ ውጪ እንዲሆን ሊገደድ ይችላል:: ይህም ኢኮኖሚን ያማከለ አመራረት መከተል ግድ እንዳለብን ያሳስበናል:: እኛ ማምረት የፈለግነው ጥሬ ሐብት ማግኘት በምንችልበት አቅራብያ በመሆን ዝቅተኛ ክፍያ የሚጠይቁ አገልግሎቶችን በመጠቀም የሰው ሐይልንና ማሽንን በአግባቡ በመጠቀም ትርፋማነትን መጨመር እንደሚችል ረዳት ፕሮፌሰር ግዛቸው ሽፈራው ሀሳባቸውን ያጋራሉ::

እንዲህና እንዲያ ነው ነገሩ :: ስለ ምን ምርት አመራረት ማወቅ ትፈልጋላቹ?! ብትኮምቱልኝ ማወቅ የምትፈልጉትን አስቀድማለው:: ወደ ፊት በምህንድስና ትምህርት የቀሰምኳቸውን ጠቃሚ ሀሳቦች አደራሳችዋለው።


ምርጫቹ አድርጋቹ ስላነበባችሁ አመሰግናለሁ::
ሐሳብ ዋጋ አለው!

#አሽሩካ